Exodus 20

ዐሥርቱ ትእዛዛት

20፥1-17 ተጓ ምብ – ዘዳ 5፥6-21 1እግዚአብሔር (ኤሎሂም) እነዚህን ቃሎች ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ፤

2“ከግብፅ ከባርነት ምድር ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) እኔ ነኝ።

3“ከእኔ በቀር
ወይም፣ ከእኔ ጋር
ሌሎች አማልክት አይኑሩህ።
4በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ነገሮች በማናቸውም ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ። 5አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) የሚጠሉኝን ልጆች ከአባቶቻቸው ኀጢአት የተነሣ እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ድረስ የምቀጣ ቀናተኛ አምላክ (ኤሎሂም) ነኝ፤ 6ነገር ግን ለሚወድዱኝና ትእዛዞቼን ለሚጠብቁ እስከ ሺሕ ትውልድ ድረስ ፍቅርን የማሳይ ነኝ።
7 የእግዚአብሔር (ያህዌ) የአምላክህን ስም ያለ አግባብ አታንሣ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስሙን ያለ አግባብ የሚያነሣውን በደል አልባ አያደርገውምና።
8የሰንበትን ቀን ቅዱስ አድርገህ አክብር። 9ስድስት ቀን ትሠራለህ፤ ሥራህንም ሁሉ አከናውን። 10ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበት ነው። በዕለቱ አንተም ሆንህ ወንድ ልጅህ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወንድ አገልጋይህ ወይም ሴት አገልጋይህ፣ ወይም እንስሳትህ፣ ወይም በግቢህ ያለ መጻተኛ ምንም ሥራ አትሠሩም። 11እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰማይንና ምድርን፤ ባሕርንና በውስጡም ያሉትን ሁሉ በስድስት ቀን ፈጥሮ፣ በሰባተኛው ቀን ዐርፏልና። ስለዚህ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሰንበትን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም።
12አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም።
13አትግደል።
14አታመንዝር።
15አትስረቅ።
16በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር።
17የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ወይም የእርሱን ወንድ አገልጋይ ሆነ ሴት አገልጋይ፣ በሬውንም ሆነ አህያውን ወይም የእርሱ የሆነውን ማናቸውንም ነገር አትመኝ።”

18ሕዝቡም መብረቁንና ነጐድጓዱን የተራራውን መጤስና የመለከቱን ድምፅ ባዩና በሰሙ ጊዜ በፍርሀት ተንቀጠቀጡ፤ በርቀትም ቆሙ፤ 19ሙሴን፣ “አንተ ራስህ ተናገረን፤ እኛም እናደምጥሃለን፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) እንዲናገረን አታድርግ፤ አለዚያ መሞታችን ነው” አሉት።

20ሙሴም ለሕዝቡ፣ “አትፍሩ፤ ኀጢአት እንዳትሠሩ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፍርሀት ከእናንተ ጋር ይሆን ዘንድ፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሊፈትናችሁ መጥቷል” አላቸው።

21እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወዳለበት ጥቅጥቅ ወደ ሆነው ጨለማ ሙሴ ቀርቦ ሳለ፣ ሕዝቡ በርቀት ቆመው ነበር።

ጣዖቶችና መሠዊያዎች

22ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “ለእስራኤላውያን ይህን ንገራቸው፤ ‘ከሰማይ ሆኜ እንደ ተናገርኋችሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል፤ 23ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሯችሁ፤ ከብር ወይም ከወርቅ ለእናንተ አማልክትን አታብጁ።

24“ ‘የጭቃ መሠዊያን ሥራልኝ፤ በእርሱም ላይ የሚቃጠልና የኅብረት መሥዋዕትን
በትውፊት፣ የሰላም መሥዋዕት በመባል ይታወቃል።
ከበጎችህ፣ ከፍየሎችህና ከቀንድ ከብቶችህ ሠዋልኝ፤ ስሜ እንዲከበር በማደርግበት ቦታ ሁሉ ወደ አንተ እመጣና እባርክሃለሁ።
25ከድንጋይ መሠዊያ የምትሠራልኝ ከሆነ፣ ከጥርብ ድንጋይ አትሥራ፤ መሣሪያ የነካው ከሆነ ታረክሰዋለህና። 26ወደ መሠዊያዬም በደረጃ አትውጣ፤ አለዚያ ኀፍረተ ሥጋህ ይገለጣል።’

Copyright information for AmhNASV